ኤርምያስ 7 NASV

ዋጋ ቢስ አምልኮ

1 ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤

2 “በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ በዚያም ይህን መልእክት ዐውጅ፤“ ‘እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሕዝብ ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3 የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።

4 ይህ ‘የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ’ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።

5 መንገዳችሁንና ሥራችሁን በእርግጥ ብታሳምሩ፣ በመካከላችሁ ቅንነት ቢኖር፣

6 መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣

7 ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ።

8 እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል።”

9 “ ‘ትሰርቃላችሁ፤ ሰው ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ በሐሰት ትምላላችሁ፤ ለበኣል ታጥናላችሁ፤ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ፤

10 ስሜ ወደ ሚጠራበት ወደዚህ ቤት መጥታችሁ በፊቴ ትቆሙና “ደህና ነን”። እያላችሁ እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ታደርጋላችሁ።

11 ስሜ የሚጠራበት፣ ይህ ቤት በእናንተ ዘንድ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፤ የምታደርጉትን ነገር አይቻለሁ ይላል እግዚአብሔር።

12 “ ‘እንግዲህ ቀድሞ የስሜ ማደሪያ አድርጌው ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትንም እዩ።

13 እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም።

14 ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ፤

15 ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’

16 “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም።

17 እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18 ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች እንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።

19 ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ “ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?

20 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈሳል፤ ይነዳል፤ አይጠፋምም።”

21 “ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን በሌሎች መሥዋዕታችሁ ላይ ጨምሩ፤ ሥጋውንም ራሳችሁ ብሉ።

22 የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ስለ መሥዋዕቶችና ስለሚቃጠል መሥዋዕት አልተናገርኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም።

23 ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝዃችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው።

24 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።

25 አባቶቻችሁ ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በየቀኑ ሳላሰልስ አገልጋዮቼን ነቢያትን ላክሁባቸው።

26 ሕዝቡ ግን አልሰማኝም፤ ልብ ብሎ ለማድመጥም አልፈለገም፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ አባቶቻቸው ከሠሩት የባሰም ክፉ አደረጉ።” ’

27 “ይህን ሁሉ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱ ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ አይመል ሱልህም።

28 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቶአል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቶአል።

29 እግዚአብሔር ቍጣው የወረደበትን ይህን ትውልድ ስለ ናቀውና ስለ ተወው፣ ጠጒርሽን ቈርጠሽ ጣይ፤ በባድሞቹ ኰረብቶች ላይ ሆነሽም ሙሾ አውጪ።

የዕርድ ሸለቆ

30 “ ‘የይሁዳ ሕዝብ በፊቴ ክፉ ነገር አድርጓል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ አስጸያፊ ነገራቸውን ስሜ በተጠራበት ቤት በማስቀመጥ አርክሰውታል።

31 እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ።

32 ስለዚህ አስተውሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ስፍራ እስከማይገኝ ድረስ ሙታንን በቶፌት ስለሚቀ ብሩ፣ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል።

33 የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም።

34 የደስታና የተድላን ድምፅ፣ የሙሽራና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም መንገዶች አጠፋለሁ፤ ምድሪቱ ባድማ ትሆናለችና።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52