ኤርምያስ 36 NASV

ኢዮአቄም የኤርምያስን ብራና አቃጠለ

1 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የነበረው ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2 “የብራና ጥቅልል ውሰድ፤ ለአንተም መናገር ከጀመርሁበት ከኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ስለ እስራኤል፣ ስለ ይሁዳና ስለ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የነገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤

3 ምናልባትም የይሁዳ ሕዝብ ላመጣባቸው ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ ሲሰሙ፣ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ክፋታቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”

4 ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራው፤ ባሮክም እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ በብራናው ላይ ጻፈ።

5 ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ አለው፤ “እኔ ተከልክያለሁና ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልችልም፤

6 ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደህ፣ በቃል እየነገርሁህ በብራናው ላይ የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን ለተሰበሰበው ሕዝብ አንብብ፤ ከየከተሞቻቸው ለመጡት ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ አንብብ።

7 እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣና መቅሠፍት ታላቅ ስለ ሆነ፣ ምናልባት ልመናቸውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”

8 የኔርያ ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ የነገረውን ሁሉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ቃል ከብራናው አነበበ።

9 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የሆነው ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ሁሉና ከይሁዳ ከተሞች የመጡት ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጾም ዐወጁ።

10 ባሮክም በብራና ላይ የተጻፈውን የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ፤ ‘አዲሱ በር’ በሚባለው በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ በሚገኘው በጸሓፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል ውስጥ ሆኖ ለሕዝቡ ሁሉ አነበበው።

11 የሳፋን ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ ከብራናው የተነበበውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ በሰማ ጊዜ፣

12 በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ጸሓፊው ክፍል ወረደ፤ በዚያም መኳንንቱ ሁሉ፦ ጸሓፊው ኤሊሳማ፣ የሸማያ ልጅ ድላያ፣ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፣ የሳፋን ልጅ ገማርያ፣ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ እንዲሁም ሌሎች መኳንንት ሁሉ ተቀምጠው ነበር።

13 ባሮክ ለሕዝቡ ከብራናው ሲያነብ ሚክያስ የሰማውን ሁሉ ከነገራቸው በኋላ፣

14 መኳንንቱ ሁሉ የኩሲን ልጅ የሴሌምያን ልጅ የናታንያን ልጅ ይሁዲን፣ “ለሕዝቡ ያነበብኸውን ብራና ይዘህ እንድትመጣ” ብለው ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ብራናውን ይዞ ወደ እነርሱ መጣ፤

15 እነርሱም፣ “እስቲ ተቀምጠህ አንብብልን” አሉት። ባሮክም አነበበላቸው፤

16 እነርሱም ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ እርስ በርሳቸው በፍርሀት በመተያየት ባሮክን፣ ይህን ሁሉ ቃል ለንጉሡ መንገር ይገባናል።” አሉት፤

17 ደግሞም፣ “ይህን ሁሉ እንዴት ልትጽፍ እንደ ቻልህ ንገረን፤ ኤርምያስ በቃል እየነገረህ ነውን?” ብለው ባሮክን ጠየቁት።

18 ባሮክም፣ “አዎን ይህን ሁሉ በቃሉ ነገረኝ፤ እኔም በብራናው ላይ በቀለም ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው።

19 መኳንንቱም ባሮክን፣ “እንግዲያውስ አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሸሸጉ፤ የት እንዳላችሁም ማንም አይወቅ” አሉት።

20 የብራናውን ጥቅልል በጸሓፊው በኤሊሳማ ክፍል ካስቀመጡት በኋላ፣ ንጉሡ ወዳለበት አደባባይ ሄደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት።

21 ንጉሡም ብራናውን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከው፤ ይሁዲም ከጸሓፊው ከኤሊሳማ ክፍል ብራናውን አምጥቶ፣ ለንጉሡና በንጉሡ አጠገብ ቆመው ለነበሩት መኳንንት ሁሉ አነበበላቸው።

22 ዘጠነኛው ወር እንደ መሆኑ፣ ንጉሡ የክረምትን ወራት በሚያሳልፍበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በምድጃ የሚነድ እሳትም ፊት ለፊቱ ነበር።

23 ይሁዲ ከብራናው ሦስት ወይም አራት ዐምድ ባነበበ ቍጥር ንጉሡ ብራናው ሁሉ እስከሚያልቅ ድረስ በጸሓፊ ቢላዋ እየቈረጠ እንዲቃጠል ወደ እሳቱ ምድጃ ይጥል ነበር።

24 ንጉሡም ሆነ ይህን ሁሉ ቃል የሰሙት መኳንንት ሁሉ አንዳች አልፈሩም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም።

25 ኤልናታን፣ ድላያ፣ ገማርያም ንጉሡ ብራናውን እንዳያቃጥል ቢለምኑትም እንኳ አልሰማቸውም፣

26 ይልቁንም ጸሓፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይዘው ያስሩ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረምሕኤልን፣ የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያንና የአብድኤልን ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፤ እግዚአብሔር ግን ሰውሮአቸው ነበር።

27 ንጉሡ፣ ባሮክ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ የጻፈው ቃል ያለበትን ብራና ካቃጠለ በኋላ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

28 “ሌላ ብራና ወስደህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤

29 ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል፤ ይህቺን ምድር፣ በእርሷም ላይ የሚኖሩትን ሰዎችንና እንስሳትን ያጠፋል በማለት የጻፍህበት ለምንድን ነው?” ብለህ ብራናውን አቃጥለሃል።

30 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፤ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከዘሩ አይገኝም፤ ሬሳውም ወደ ውጭ ተጥሎ ለቀን ሐሩርና ለሌት ቍር ይጋለጣል።

31 እርሱንና ልጆቹን መኳንንቱንም ስለ ክፋታቸው እቀጣለሁ፤ አልሰሙኝምና አመጣባቸዋለሁ ያልሁትን ጥፋት ሁሉ በእነርሱና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት፣ በይሁዳም ሕዝብ ላይ አመጣለሁ።’ ”

32 ኤርምያስም ሌላ ብራና ወስዶ ለኔርያ ልጅ ለጸሓፊው ለባሮክ ሰጠው፤ ባሮክም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ባቃጠለው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ ጻፈበት፤ ብዙ ተመሳሳይ ቃልም ተጨመረበት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52