ኤርምያስ 35 NASV

የሬካባውያን ታማኝነት

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ፣ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ የሚል ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2 “ወደ ሬካባውያን ሄደህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣቸው፤ ወደ አንዱም ክፍል አስገብተህ የሚጠጡትን ወይን ጠጅ ስጣቸው።”

3 ስለዚህ የካባስን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን፣ ወንድሞቹንና ወንዶች ልጆቹን ሁሉ፣ የሬካባውያንን ወገን በአጠቃላይ ሄጄ ጠራኋቸው፤

4 ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣኋቸው፤ ወደ ሐናን ልጆች ክፍልም አስገባኋቸው፤ የሐናን አባት ጌዴልያም የእግዚአብሔር ሰው ነበረ። ክፍሉም በመኳንንቱ ክፍል አጠገብ፣ ከመዕሤያ ክፍል በላይ ነበር፤ መዕሤያም የበር ጠባቂው የሰሎም ልጅ ነበረ፤

5 በሬካባውያንም ሰዎች ፊት በወይን ጠጅ የተሞሉ ማድጋዎችን አቀረብሁ፤ ዋንጫዎችንም ሰጥቻቸው፣ “በሉ፤ የወይን ጠጅ ጠጡ” አልኋቸው።

6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናል፤ ‘እናንተና ዘራችሁ ከቶ የወይን ጠጅ አትጠጡ፤

7 ቤት አትሥሩ፤ ዘር አትዝሩ፤ ወይን አትትከሉ፤ ሁል ጊዜ በድንኳን ኑሩ እንጂ ከእነዚህ ነገሮች አንዱም አይኑራችሁ፤ ይህም ሲሆን እንደ መጻተኛ በሆናችሁበት ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።’

8 እኛም አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ ፈጽመናል፤ እኛና ሚስቶቻችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም የወይን ጠጅ ጠጥተን አናውቅም፤

9 የምንቀመ ጥበትም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታ፣ የዕርሻ ስፍራ ወይም የእህል ዘር የለንም።

10 በድንኳን ኖረናል፤ አባታችን ኢዮናዳብ ያዘዘንንም ሁሉ ጠብቀናል።

11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆር ይህችን ምድር በወረረ ጊዜ፣ ኑ፤ ከባቢሎን ሰራዊትና ከሶርያ ሰራዊት ሸሽተን ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ’ ተባባልን፤ ስለዚህም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።”

12 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

13 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሂድ፤ ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ቃሌን ትጠብቁ ዘንድ ከዚህ አትማሩምን?’ ይላል እግዚአብሔር፤

14 ‘የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አዘዛቸው፤ ይህም ትእዛዝ ተጠብቆአል፤ የአባታቸውን ትእዛዝ ስለ ጠበቁ እስከ ዛሬ ድረስ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤ እናንተ ግን እኔ ደጋግሜ ብናገራችሁም፤ አልታዘዛችሁኝም።

15 አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ወደ እናንተ ላክሁ፤ እነርሱም፣ “እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ምግባራችሁን አስተካክሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖሩ ዘንድ ሌሎቹን አማልክት ለማገልገል አትከተሉ” አልኋችሁ። እናንተ ግን ጆሮአችሁን ወደ እኔ አላዘነበላችሁም፤ አልሰማችሁኝምም።

16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ዘሮች አባታቸው የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠብቀዋል፤ ይህ ሕዝብ ግን አልታዘዘኝም።’

17 “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አደርሳለሁ ያልሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ፤ በተናገርኋቸው ጊዜ፣ አልሰሙኝምና በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝም።’ ”

18 ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአባታችሁን የኢዮናዳብን ትእዛዝ ስለ ጠበቃችሁ፤ መመሪያውን ስለ ተከተላችሁ፤ ያዘዛችሁንም ሁሉ ስለ ፈጸማችሁ’

19 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን የሚያገለግለኝ ሰው ለዘላለም አይታጣም።’ ”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52