1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮስያስን ልጅ ሴዴቅያስን በይሁዳ ላይ አነገሠው፤ እርሱም በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፈንታ ነገሠ።
2 ነገር ግን እርሱም ሆነ መኳንንቱ የምድሪቱም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
3 ንጉሡ ሴዴቅያስም፣ “ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ” በማለት የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ።
4 ኤርምያስ ገና እስር ቤት ስላልገባ፣ በሕዝቡ መካከል እንደ ልቡ ይወጣና ይገባ ነበር።
5 የፈርዖንም ሰራዊት ከግብፅ ወጥቶ ነበርና ኢየሩሳሌምን ከበው የነበሩት ባቢሎናውያን ይህን ሲሰሙ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ።
6 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
7 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትጠይቁኝ ዘንድ ወደ እኔ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሰራዊት ወደ ገዛ አገሩ ወደ ግብፅ ይመለሳል፤
8 ባቢሎናውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይወጓታል፤ ይዘውም ያቃጥሏታል።’
9 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ባቢሎናውያን በእርግጥ ትተውን ይሄዳሉ’ ብላችሁ አታስቡ፤ አይሄዱምና ራሳችሁን አታታሉ።
10 የሚዋጋችሁን የባቢሎናውያንን ሰራዊት ሁሉ አሸንፋችሁ፣ ቍስለኞች ብቻ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ቢቀሩ እንኳ፤ እነዚህ ሰዎች መጥተው ይህችን ከተማ ያቃጥሏታል።”
11 የባቢሎን ሰራዊት ከፈርዖን ጭፍራ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ከወጣ በኋላ፣
12 ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን ድርሻ ለመካፈል፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ተነሣ፤
13 ነገር ግን ወደ ብንያም በር ሲደርስ፣ የዘበኞች አለቃ የነበረው የሐናንያ ልጅ የሴሌምያ ልጅ የሪያ የተባለው፣ “ከድተህ ወደ ባቢሎናውያን ልትሄድ ነው!” በማለት ያዘው።
14 ኤርምያስም፣ “ሐሰት ነው! ከድቼ ወደ ባቢሎናውያን መሄዴ አይደለም” አለ፤ የሪያ ግን አልሰማውም፤ እንዲያውም ኤርምያስን አስሮ ወደ መኳንንቱ አመጣው።
15 መኳንንቱም እጅግ ተቈጥተው ኤርምያስን ደበደቡት፤ የግዞት ቤትም አድርገውት በነበረው፤ በጸሓፊው በዮናታን ቤት አሰሩት።
16 ኤርምያስም በምድር ቤት በሚገኝ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ ተደረገ፤ በዚያም ረጅም ጊዜ ቈየ።
17 ከዚያም በኋላ ንጉሡ ሴዴቅያስ ላከበትና ወደ ቤተ መንግሥት አስመጣው፤ ለብቻውም ወስዶ፣ “ከእግዚአብሔር የመጣ ቃል አለህ?” በማለት ጠየቀው።ኤርምያስም፣ “አዎን አለ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፈህ ትሰጣለህ” አለው።
18 ኤርምያስም ንጉሡ ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፤ “ያሰራችሁኝ በአንተና በመኳንንትህ ወይም በዚህ ሕዝብ ላይ ምን ወንጀል ፈጽሜ ነው?
19 ለመሆኑ፣ ‘የባቢሎን ንጉሥ እናንተንም ይህችንም ምድር አይወጋም’ ብለው ትንቢት ይናገሩ የነበሩት ነቢያታችሁ ወዴት ናቸው?
20 አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ አድምጠኝ፤ ልመናዬን በፊትህ ላቅርብ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሓፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።”
21 ንጉሡም ሴዴቅያስ፣ ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ እንዲቀመጥና በከተማዪቱ ያለው እንጀራ እስኪያልቅ ድረስ ከእንጀራ ጋጋሪዎች ሰፈር በየቀኑ አንድ አንድ እንጀራ እንዲሰጠው አዘዘ፤ ስለዚህ ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀመጠ።