ኤርምያስ 4 NASV

1 “እስራኤል ሆይ፤ ብትመለስ፣ወደ እኔ ብትመለስ፤”ይላል እግዚአብሔር፤“አስጸያፊ ነገሮችህን ከፊቴ ብታስወግድ፣ባትናወጥ ብትቆምም፣

2 በእውነት፣ በቅንነትና በጽድቅ፣‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለህ ብትምል፣አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ፤በእርሱም ይከበራሉ።”

3 እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ያላል፤“ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤በእሾህም መካከል አትዝሩ።

4 እናንተ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች፤ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤አለዚያ ስለ ሠራችሁት ክፋት፣ቍጣዬ እንደ እሳት ይንበለበላል፤ሊገታውም የሚችል የለም።

ጥፋት ከሰሜን መምጣቱ

5 “ ‘በምድሪቱ ሁሉ መለከትን ንፉ’ ብላችሁ፤በይሁዳ ተናገሩ፣ በኢየሩሳሌም ዐውጁ፤ጩኹ፤ እንዲህም በሉ፤‘በአንድነት ተሰብሰቡ፤ወደ ተመሸጉት ከተሞች እንሽሽ’

6 ወደ ጽዮን ለመግባት ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ቶሎ ሸሽታችሁ አምልጡ፤ከሰሜን መቅሠፍትን፣ታላቅ ጥፋትን አመጣለሁና።”

7 አንበሳ ከደኑ ወጥቶአል፤ሕዝብንም የሚያጠፋ ተሰማርቶአል፤ምድርሽን ባዶ ሊያደርግ፣ከስፍራው ወጥቶአል።ከተሞችሽ ፈራርሰው ይወድቃሉ፤ያለ ነዋሪም ይቀራሉ።

8 ስለዚህ ማቅ ልበሱ፤እዘኑ፤ ዋይ በሉ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቍጣ፣ከእኛ አልተመለሰምና።

9 ‘ “በዚያ ቀን” ይላል እግዚአብሔር፤“ንጉሡና ሹማምቱ ወኔ ይከዳቸዋል፤ካህናቱ ድንጋጤ ይውጣቸዋል፤ነቢያቱም ብርክ ይይዛቸዋል።”

10 እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰይፍ አንገታቸው ላይ ተቃጥቶ ሳለ፣ ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ለምን እጅግ አታለልህ?” አልሁ።

11 በዚያን ጊዜ፣ ለእዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ተብሎ ይነገራል፤ “ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን፣ ከዚያ የበረታ የሚጠብስ ደረቅ ነፋስ በምድረ በዳ ካሉት ባድማ ኰረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ

12 በእኔ ትእዛዝ ይነፍሳል፤ እንግዲህ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።”

13 እነሆ፤ እንደ ደመና ይንሰራፋል፤ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣሉ፤ፈረሶቹም ከንስር ይፈጥናሉ፤መጥፋታችን ነውና ወዮልን!

14 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እንድትድኚ ከልብሽ ክፋት ታጠቢ፤እስከ መቼ ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ ይኖራል?

15 ድምፅ ከዳን ይሰማልና፤ከኤፍሬም ተራሮችም ጥፋትን ያውጃል።

16 “ይህን ለሕዝቦች አሳውቁ፤ለኢየሩሳሌምም እንዲህ ብላችሁ በይፋ ንገሩ፤‘ከበው የሚያስጨንቁ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤በይሁዳ ከተሞችም ላይ ይደነፋሉ፤

17 ሰብል እንደሚጠብቁ ሰዎች ይከቧታል፤በእኔ ላይ ዐምፃለችና፤’ ”ይላል እግዚአብሔር።

18 “የገዛ መንገድሽና ተግባርሽ፣ይህን አምጥቶብሻል፤ይህም ቅጣትሽ ነው፤ምንኛ ይመራል!እንዴትስ ልብ ይሰብራል!”

19 ወይ አበሳዬ! ወይ አበሳዬ!ሥቃይ በሥቃይ ላይ ሆነብኝ፤አወይ፣ የልቤ ጭንቀት!ልቤ ክፉኛ ይመታል፤ዝም ማለት አልችልም፤የመለከትን ድምፅ፣የጦርነትንም ውካታ ሰምቻለሁና።

20 ጥፋት በጥፋት ላይ ይመጣል፤ምድሪቱም በሞላ ባድማ ትሆናለች፤ድንኳኔ በድንገት፣መጠለያዬም በቅጽበት ጠፋ።

21 እስከ መቼ የጦርነት ዐርማ እመለከታለሁ?እስከ መቼስ የመለከት ድምፅ እሰማለሁ?

22 “ሕዝቤ ተላሎች ናቸው፤እኔን አያውቁኝም።ማስተዋል የጐደላቸው፣መረዳትም የማይችሉ ልጆች ናቸው።ክፋትን ለማድረግ ጥበበኞች፤መልካም መሥራት ግን የማያውቁ።”

23 ምድርን ተመለከትሁ፤እነሆ ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፤ሰማያትንም አየሁ፣ብርሃናቸው ጠፍቶአል።

24 ተራሮችን ተመለከትሁ፣እነሆ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ኰረብቶችም ሁሉ ተናጡ።

25 አየሁ፤ ሰው አልነበረም፤የሰማይ ወፎች ሁሉ በረው ጠፍተዋል።

26 ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ፍሬያማው ምድር በረሓ ሆነ፤ከተሞቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት፣ከብርቱ ቍጣው የተነሣ ፈራረሱ።

27 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፤ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም።

28 ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፤ሰማያትም በላይ ይጨልማሉ፤ተናግሬአለሁ፤ ሐሳቤን አልለውጥም፤ወስኛለሁ፤ ወደ ኋላም አልልም።

29 ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ጩኸት የተነሣ፣ከተማ ሁሉ ይሸሻል፤አንዳንዶች ደን ውስጥ ይገባሉ፤ሌሎችም ቋጥኝ ላይ ይወጣሉ፤ከተሞች ሁሉ ባዶ ቀርተዋል፤የሚኖርባቸውም የለም።

30 አንቺ ለጥፋት የተዳረግሽ ሆይ፤ ምን መሆንሽ ነው?ቀይ ቀሚስ የለበስሽው ለምንድ ነው?ለምን በወርቅ አጌጥሽ?ዐይኖችሽንስ ለምን ተኳልሽ?እንዲያው በከንቱ ተሽሞንሙነሻል፤የተወዳጀሻቸው ንቀውሻልና፤ነፍስሽንም ሊያጠፉ ይፈልጋሉ።

31 የበኵር ልጇን ለመውለድ እንደምታምጥ፣በወሊድ እንደምትጨነቅ ሴት ድምፅ ሰማሁ፤የጽዮን ሴት ልጅ ትንፋሽ አጥሮአት ስትጮኽ፣እጇን ዘርግታ፣“ወዮልኝ! ተዝለፈለፍሁ፣በነፍሰ ገዳዮች እጅ ወደቅሁ” ስትል ሰማሁ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52