1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ በባቢሎንና በምድሯ ላይ፣የሚያጠፋ ነፋስ አስነሣለሁ።
2 እንዲያበጥሯትና እንዲያወድሟት፣ባዕዳንን በባቢሎን ላይ እልካለሁ፤በመከራዋም ቀን፣ከበው ያስጨንቋታል።
3 ቀስተኛው ቀስቱን እስኪገትር፣የጦር ልብሱንም እስኪለብስ ፋታ አትስጡት፤ለወጣቶቿ አትዘኑ፤ሰራዊቷንም ፈጽማችሁ አጥፉ።
4 በባቢሎን ምድር ታርደው፣በአደባባዮቿም እስከ ሞት ቈስለው ይወድቃሉ።
5 ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ፊት፣በበደል የተሞላች ብትሆንም፣እስራኤልንና ይሁዳን አምላካቸው፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር አልጣላቸውም።
6 “ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡፈጥናችሁም ሕይወታችሁን አትርፉ!በኀጢአቷ ምክንያት አትጥፉ። የእግዚአብሔር የበቀል ጊዜ ነው፤እርሱም የሥራዋን ይከፍላታል።
7 ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ምድርንም ሁሉ አሰከረች።ሕዝቦች ከወይን ጠጇ ጠጡ፤ስለዚህ አሁን አብደዋል።
8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ትሰበራለች፤ዋይ በሉላት!ምናልባት ልትፈወስ ስለምትችል፣ለቍስሏ የሚቀባ መድኀኒት ፈልጉላት።
9 “ ‘ባቢሎንን ለመፈወስ ሞክረን ነበር፤እርሷ ግን ልትፈወስ አትችልም፤ፍርዷ እስከ ሰማይ ስለ ደረሰ፣እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ስላለ፣ትተናት ወደየአገራችን እንሂድ።’
10 “ ‘እግዚአብሔር ቅንነታችንን መሰከረ፤ኑ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ያደረገውን፣በጽዮን እንናገር።’
11 “ፍላጾችን ሳሉ፤ጋሻዎችን አዘጋጁ፤ የእግዚአብሔር ሐሳብ ባቢሎንን ለማጥፋት ስለ ሆነ፣የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቶአል፤ እግዚአብሔር ይበቀላል፤ስለ ቤተ መቅደሱ ይበቀላል።
12 በባቢሎን ቅጥር ላይ ዐላማ አንሡጥበቃውን አጠናክሩ፤ዘብ ጠባቂዎችን አቁሙ፤ደፈጣ ተዋጊዎችን አዘጋጁ እግዚአብሔር በባቢሎን ሕዝብ ላይ የወሰነውን፣ዐላማውን ያከናውናል።
13 አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቶአል፤ፍጻሜሽ ደርሶአል።
14 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፤ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሰራዊት ያጥለቀልቅሻል፤እነርሱም በድል አድራጊነት በላይሽ ያቅራራሉ።
15 “ምድርን በኀይሉ የሠራ፣ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።
16 ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።
17 “እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስ የላቸውም።
18 እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፣ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።
19 የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደ እነዚህ አይደለም፤እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
20 “አንቺ የእኔ ቈመጥ፣የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤በአንቺ ሕዝቦችን እሰባብራለሁ፤በአንቺ መንግሥታትን አጠፋለሁ፤
21 በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ሠረገላውንና ሠረገላ ነጂውን እሰባብራለሁ፤
22 በአንቺ ወንዱንና ሴቱን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ሽማግሌውንና ወጣቱን እሰባብራለሁ።በአንቺ ጐረምሳውንና ኰረዳዪቱን እሰባብራለሁ።
23 በአንቺ እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፣በአንቺ ገበሬውንና በሬውን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ገዦችንና ባለ ሥልጣኖችን እሰባብራለሁ።
24 “በጽዮን ላይ ስላደረሱት ጥፋት ሁሉ ለባቢሎንና በባቢሎን ለሚኖሩት ሁሉ ዐይናችሁ እያየ ዋጋቸውን እከፍላቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
25 “አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣አጥፊ ተራራ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣”ይላል እግዚአብሔር፤“እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ከገመገም ቍልቍል አንከባልልሻለሁ፤የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።
26 ከአንቺ ለማእዘን የሚሆን ድንጋይ፣ለመሠረትም የሚሆን ዐለት አይወሰድም፤ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ፤”ይላል እግዚአብሔር።
27 “በምድር ሁሉ ላይ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ!በሕዝቦች መካከል መለከትን ንፉ!ሕዝቦችን ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤የአራራትን፣ የሚኒንና የአስከናዝን መንግሥታት፣ጠርታችሁ በእርሷ ሰብስቡአቸው፤የጦር አዝማች ሹሙባት፤ፈረሶችንም እንደ አንበጣ መንጋ ስደዱባት።
28 የሜዶንን ነገሥታት፣ገዦቿንና ባለሥልጣኖቿን ሁሉ፣በግዛታቸው ሥር ያሉትን አገሮች ሁሉ፣እነዚህን ሕዝቦች ለጦርነት አዘጋጁባት።
29 ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።
30 የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤ኀይላቸው ተሟጦአል፤እንደ ሴት ሆነዋል፤በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሶአል፤የደጇም መወርወሪያ ተሰብሮአል።
31 ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ መያዟን፣ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር፣አንዱ ወሬኛ ሌላውን ወሬኛ፣አንዱ መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ወዲያው ወዲያው ይከተላል፤
32 መልካዎቿ እንደተያዙ፣የወንዝ ዳር ምሽጎቿ እንደ ተቃጠሉ፣ወታደሮቿም እንደ ተደናገጡ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።”
33 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣የእህል መውቂያ አውድማ ናት፤የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።
34 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላን፣አድቅቆ ፈጨን፤እንደ ባዶ ማድጋ አደረገን፤እንደ ዘንዶ ዋጠን፣እንደ ጣፋጭ በልቶን ሆዱን ሞላ፤በኋላም አንቅሮ ተፋን፤
35 የጽዮን ነዋሪዎች፣ እንዲህ ይላሉ፤“በሥጋችን ላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን፤”ኢየሩሳሌም እንዲህ ትላለች፤“ደማችን በባቢሎን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን።”
36 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ እሟገትልሻለሁ፣በቀልሽንም እኔ እበቀልልሻለሁ፤ባሕሯን አደርቃለሁ፣የምንጮቿንም ውሃ።
37 ባቢሎን የፍርስራሽ ክምር፣የቀበሮዎች መፈንጫ፣የድንጋጤና የመሣለቂያ ምልክት ትሆናለች፤የሚኖርባትም አይገኝም።
38 ሕዝቦቿ ሁሉ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤እንደ አንበሳ ግልገልም ያጒረመርማሉ።ጒሮሮአቸው በደረቀ ጊዜድግስ አዘጋጅላቸዋለሁ፤እንዲሰክሩም አደርጋቸውና፤”
39 በሣቅ እየፈነደቁ፣ለዘላለም ላይነቁ ይተኛሉ።”ይላል እግዚአብሔር።
40 “እንደ ጠቦት፣እንደ አውራ በግና እንደ ፍየል፣ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።
41 “ሼሻክ እንዴት ተማረከች!የምድር ሁሉ ትምክህትስ እንዴት ተያዘች!ባቢሎን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ፣ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች።
42 ባሕር በባቢሎን ላይ ይወጣል፤ሞገዱም እየተመመ ይሸፍናታል።
43 ከተሞቿ ሰው የማይኖርባቸው፣ዝርም የማይልባቸው፣ደረቅና በረሓማ ቦታ፣ባድማ ምድርም ይሆናሉ።
44 ቤልን በባቢሎን ውስጥ እቀጣለሁ፤የዋጠውን አስተፋዋለሁ፤ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደ እርሱ አይጐርፉም፤የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።
45 “ሕዝቤ ሆይ፤ ከመካከሏ ውጡሕይወታችሁን አትርፉ!ከአስፈሪው የእግዚአብሔር ቍጣ አምልጡ።
46 ወሬ በምድሪቱ ሲሰማ፣ተስፋ አትቍረጡ፤ አትፍሩም፤ገዥ በገዥ ላይ ስለ መነሣቱ፣ዐመፅም በምድሪቱ ስለ መኖሩ፣አንድ ወሬ ዘንድሮ፣ ሌላውም ለከርሞ ይመጣል፤
47 የባቢሎንን ጣዖታት የምቀጣበት ጊዜ፣በርግጥ ይመጣልና።ምድሯ በሙሉ ትዋረዳለች፤የታረዱትም በሙሉ በውስጧ ይወድቃሉ።
48 ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፤አጥፊዎች ከሰሜን ወጥተው፣እርሷን ይወጓታልና፤”ይላል እግዚአብሔር።
49 “በምድር ሁሉ የታረዱት፣በባቢሎን ምክንያት እንደ ወደቁ፣ባቢሎንም በእስራኤል በታረዱት ምክንያት መውደቅ ይገባታል።
50 ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፤ሂዱ! ጊዜ አትፍጁ፤በሩቅ ምድር ያላችሁ እግዚአብሔርን አስታውሱ፤ኢየሩሳሌምንም አስቧት።”
51 “ባዕዳን ሰዎች ወደ ተቀደሰው፣ወደ እግዚአብሔር ቤት ስለ ገቡ፣እኛ ተሰድበናል፤ዕፍረትም ፊታችንን ሸፍኖአል፤ውርደትም ተከናንበናል።”
52 “እንግዲህ ጣዖቶቿን የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር፤“በምድሯም ሁሉ፤ቍስለኞች ያቃስታሉ።
53 ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣም፣ከፍ ያለ ምሽጓን ብታጠናክርም፣አጥፊዎች እሰድባታለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።
54 “ከባቢሎን ጩኸት፣ከባቢሎናውያንምየ ምድር፣የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል።
55 እግዚአብሔር ባቢሎንን ያጠፋታል፤ታላቅ ጩኸቷንም ጸጥ ያደርጋል።ሞገዳቸው እንደ ታላቅ ውሃ ይተማል፤ጩኸታቸውም ያስተጋባል።
56 በባቢሎን ላይ አጥፊ ይመጣል፤ጦረኞቿ ይማረካሉ፤ቀስታቸውም ይሰበራል፤ እግዚአብሔር ግፍን የሚበቀል፣ተገቢውንም ሁሉ የሚከፍል አምላክ ነውና።
57 ባለ ሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤”ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ።
58 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ወፍራሙ የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤ከፍ ያሉት ደጆቿም በእሳት ይቃጠላሉ፤ሰዎቹ በከንቱ ይደክማሉ፤የሕዝቡም ልፋት ለእሳት ይሆናል።”
59 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የንጉሡ የግቢ አስከልካይ የነበረው የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ ከንጉሡ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ የሰጠው መልእክት ይህ ነው።
60 ኤርምያስ ስለ ባቢሎን ጽፎ ያስቀመጠውን ሁሉ፣ በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት ሁሉ በብራና ጥቅልል ላይ ጻፈው፤
61 ለሠራያም እንዲህ አለው፤ “ባቢሎን በደረስህ ጊዜ፣ ይህን ቃል ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብ አትዘንጋ
62 እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህችን ስፍራ ሰውም ሆነ እንስሳ እስከማይኖርባት ድረስ ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ ብለሃል።’
63 ይህን ብራና አንብበህ ከጨረስህ በኋላ፣ ድንጋይ አስረህበት ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ጣለው፤
64 እንዲህም በል፤ ‘ባቢሎንም እኔ ከማመጣባት ጥፋት የተነሣ፣ እንደዚሁ ትሰጥማለች፤ ከእንግዲህም አትነሣም፤ ሕዝቧም ይወድቃል።’ ”