ኤርምያስ 5 NASV

ቅን ሰው አለመገኘቱ

1 “በኢየሩሳሌም መንገዶች እስቲ ውጡ፤ ወደ ላይ ወደታችም ውረዱ፤ዙሪያውን ተመልከቱ ቃኙ፤በአደባባይዋም ፈልጉ፤እውነትን የሚሻና በቅንነት የሚሄድ፣አንድ ሰው እንኳ ብታገኙ፣እኔ ይህቺን ከተማ እምራታለሁ።

2 ‘ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉም፣የሚምሉት በሐሰት ነው።”

3 እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህ እውነትን አይመለከቱምን?አንተ መታሃቸው፤ እነርሱ ግን አልተሰማቸውም፤አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን አልታረሙም፤ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠነከሩበንስሓ ለመመለስም አልፈለጉም።

4 እኔም በልቤ እንዲህ አልሁ፤ “እነዚህ ድኾች ናቸው፤ሞኞች ናቸው፤ የእግዚአብሔርን መንገድ፣የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና።

5 ስለዚህ ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ፤ለእነርሱም እናገራለሁ፤በእርግጥ እነርሱ የእግዚአብሔርን መንገድ፣የአምላካቸውንም ሕግ ያውቃሉና።”ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ ያው እንደዚያው ቀንበሩን ሰብረዋል፤እስራቱንም በጥሰዋል።

6 ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰባብራቸዋል፣የበረሓ ተኵላም ይቦጫጭቃቸዋል፤ብቅ የሚለውን ሰው ሁሉ ለመገነጣጠል፣ነብር በከተሞቻቸው ዙሪያ ያደባል፤ዐመፃቸው ታላቅ፣ክሕደታቸው ብዙ ነውና።

7 “ታዲያ፣ እንዴት ይቅር ልልሽ እችላለሁ?ልጆችሽ ትተውኛል፤እውነተኛውን አምላክ ትተው አማልክት ባልሆኑት ምለዋል፤እስኪጠግቡ ድረስ መገብኋቸው፤እነርሱ ግን አመነዘሩ፤ወደ ጋለሞቶችም ቤት ተንጋጉ።

8 እንደ ተቀለበ ብርቱ ድንጒላ ፈረስ ሆኑ፤እያንዳንዱም የሌላውን ሚስት ተከትሎ አሽካካ።

9 ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀጣቸውምን?”ይላል እግዚአብሔር።“እኔ ራሴ እንደዚህ ዐይነቱን ሕዝብ፣አልበቀልምን?

10 “ወደ ወይን አትክልቷ ስፍራ ገብታችሁ አበላሹት፤ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉት፤ቅርንጫፎቿን ገነጣጥሉ፤ የእግዚአብሔር አይደሉምና፤

11 የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት፣ፈጽመው ከድተውኛል፤”ይላል እግዚአብሔር።

12 በእግዚአብሔር ላይ ሐሰትን ተናገሩ፤እንዲህም አሉ፤ “እሱ ምንም አያደርግም!ክፉ ነገር አይደርስብንም፤ሰይፍም ራብም አናይም፤

13 ነቢያቱ ነፋስ እንጂ ሌላ ነገር አይደሉም፤ቃሉም በውስጣቸው የለም፤ያሉት ሁሉ በእነርሱ ላይ ይመለስ።”

14 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሕዝቡ ይህን ቃል ስለ ተናገረ፣ቃሌን በአፍህ ውስጥ የሚፋጅ እሳት፣ይህንም ሕዝብ ማገዶ አደርጋለሁ፤እሳቱም ይበላቸዋል።

15 የእስራኤል ቤት ሆይ፣” ይላል እግዚአብሔር፤“ከሩቅ ሕዝብን አመጣባችኋለሁ፤ጥንታዊና ብርቱ፣ቋንቋውን የማታውቁት፣ ንግግሩንምየማትረዱት ሕዝብ ነው።

16 የፍላጻቸው ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎች ናቸው።

17 ሰብልህንና ምግብህን ጠራርገው ይበሉብሃል፤ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን ይውጣሉ፣በጎችህንና ከብቶችህን ይፈጃሉ፤የወይን ተክሎችህንና የበለስ ዛፎችህን ያወድማሉ፤የታመንህባቸውንም የተመሸጉ ከተሞች፣በሰይፍ ያጠፉአቸዋል።

18 “ይሁን እንጂ፣ በዚያን ዘመን እንኳ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ፈጽሜ አላጠፋችሁም።

19 ሕዝቡ፣ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ሁሉ ነገር ለምን አደረገብን?’ ብለው ቢጠይቁ ‘እኔን፣ እንደ ተዋችሁኝና በራሳችሁ ምድር ባዕዳን አማልክትን እንዳገለገላችሁ፣ እንደዚሁ የእናንተ ባልሆነ ምድር ባዕዳንን ታገለግላላችሁ’ ትላቸዋለህ።

20 “በያዕቆብ ቤት ይህን አሰሙ፣በይሁዳም እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤

21 እናንት ዐይን እያላችሁ የማታዩ፣ጆሮ እያላችሁ የማትሰሙ፣ሞኞችና የማታስተውሉ ሰዎች ይህን ስሙ፤

22 ልትፈሩኝ አይገባችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር፤“በእኔ ፊት ልትንቀጠቀጡስ አይገባምን?ለዘላለም ዐልፎት መሄድ እንዳይችል፣አሸዋን ለባሕር ድንበር አደረግሁ፤ማዕበሉ እየጋለበ ቢመጣ ከዚያ አያልፍም፤ሞገዱ ቢጮኽም ሊያቋርጠው አይችልም።

23 ይህ ሕዝብ ግን የሸፈተና እልከኛ ልብ አለው፤መንገድ ለቆ ሄዶአል፤

24 በልባቸውም፣‘የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚያዘንበውን፣መከርን በወቅቱ የሚያመጣልንን፣አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ’ አላሉም።

25 በደላችሁ እነዚህን አስቀርቶባችኋል።ኀጢአታችሁ መልካሙን ነገር ከልክሎአችኋል።

26 “በሕዝቤ መካከል ክፉ ሰዎች አሉና፤ወፍ እንደሚያጠምዱ ሰዎች፣ወጥመድ ዘርግተው ሰው እንደሚይዙ ሰዎችም ያደባሉ።

27 ወፎች እንደሞሉት ጐጆ፣ቤታቸው በማጭበርበር የተሞላ ነው፤ባለጠጎችና ኀያላን ሆነዋል፤

28 ወፍረዋል፤ ሰብተዋልም።ክፋታቸው ገደብ የለውም፤ወላጅ የሌላቸው ፍትሕ እንዲያገኙአልቆሙላቸውም፤ለድኾችም መብት አልተከራከሩም።

29 ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?”ይላል እግዚአብሔር።እንዲህ ዐይነቶቹን ሕዝብ፣እኔ ራሴ ልበቀላቸው አይገባኝምን?

30 “የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ነገር፣በምድሪቱ ላይ ሆኖአል፤

31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ካህናት በነቢያቱ ምክር ያስተዳድራሉ፤ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ይወዳሉ፤ፍጻሜው ሲደርስ ግን ምን ታደርጉ ይሆን?

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52