1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የኢዮአቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንንና ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም የይሁዳን አናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር ሁለት ቅርጫት በለስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ተቀምጦ አሳየኝ።
2 አንዱ ቅርጫት፣ ቶሎ የደረሰ ፍሬ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፣ በሌላው ቅርጫት ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ የማይቻል እጅግ መጥፎ በለስ ነበረበት።
3 እግዚአብሔርም፣ “ኤርምያስ ሆይ፤ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።እኔም፣ “በለስን አያለሁ፤ ጥሩ የሆነው እጅግ መልካም ነው፤ የተበላሸው ግን እጅግ መጥፎ በመሆኑ ሊበላ የማይችል ነው” አልሁ።
4 እንደ ገናም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
5 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎናውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳ ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ።
6 ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
7 እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
8 “ ‘ነገር ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ እንደ ማይቻለው እንደ መጥፎ በለስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የቀሩትንም ሆነ በግብፅ የሚኖሩትን፣ እንዲሁ አደርግባቸዋለሁ።
9 በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉና የሚሰደቡ ይሆናሉ፤ በምበትናቸውም ስፍራ ሁሉ ለማላገጫና ለመተረቻ፣ ለመሣለቂያና ለርግማን አደርጋቸዋለሁ።
10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ ሰይፍ፣ ራብና መቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ።