1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “ሂድና ጮኸህ ይህን ለኢየሩሳሌም ጆሮ አሰማ፤“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤‘በወጣትነትሽ ጊዜ የነበረሽን ታማኝነት፣በሙሽርነትሽም ወራት እንዴት እንደ ወደድሽኝ፣በምድረ በዳ ዘር በማይዘራበት ምድር፣እንዴት እንደተከተልሽኝ አስታውሳለሁ።
3 እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረች፤የመከሩም በኵር ነበረች፤የዋጧት ሁሉ በደለኞች ሆኑ፤መዓትም ደረሰባቸው’ ”ይላል እግዚአብሔር።
4 የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ወገን ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“አባቶቻችሁ ከእኔ የራቁት፣ከንቱ ነገርን የተከተሉት፣ራሳቸውም ከንቱ የሆኑት፣ምን ጥፋት አግኝተውብኝ ነው?
6 እነርሱም፣ ‘ከግብፅ ምድር ያወጣን፣በወና ምድረ በዳ፣በጐድጓዳና በበረሓ መሬት፣በደረቅና በጨለማ ቦታ፣ሰው በማያልፍበትና በማይኖርበት ስፍራ፣የመራን እግዚአብሔር ወዴት ነው?’ ብለው አልጠየቁም።
7 እኔ፣ ፍሬዋንና በረከቷን እንድትበሉ፣ለም ወደ ሆነ መሬት አመጣኋችሁ፤እናንተ ግን መጥታችሁ ምድሬን አረከሳችሁ፤ርስቴንም ጸያፍ አደረጋችሁ።
8 ‘እግዚአብሔር ወዴት ነው?’ ብለው፣ካህናቱ አልጠየቁም፤ከሕጉ ጋር የሚውሉት አላወቁኝም፤መሪዎቹ ዐመፁብኝ፤ነቢያቱም በበኣል ስም ተነበዩ፤ከንቱ ነገሮችን ተከተሉ።
9 “ስለዚህ እንደ ገና ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፤”“ከልጅ ልጆቻችሁም ጋር እከራከራለሁ።ይላል እግዚአብሔር።
10 ወደ ኪቲም ጠረፍ ተሻገሩና እዩ፤ወደ ቄዳርም ልካችሁ በጥንቃቄ መርምሩ፣እንዲህ ዐይነት ነገር ተደርጎ ያውቅ እንደሆነ ተመልከቱ፤
11 የእውነት አማልክት ባይሆኑም እንኳ፣አማልክቱን የለወጠ ሕዝብ አለን?ሕዝቤ ግን ክብራቸውሠ የሆነውን፣በከንቱ ነገር ለወጡ።
12 ሰማያት ሆይ፤ በዚህ ተገረሙ፤በታላቅ ድንጋጤም ተንቀጥቀጡ፤”ይላል እግዚአብሔር።
13 “ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል፣ሕያው የውሃ ምንጭ የሆንሁትን፣እኔን ትተዋል፤ውሃ መያዝ የማይችሉትን ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች፣ለራሳቸው ቈፍረዋል።
14 እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውልድ ባሪያ?ታዲያ፣ ስለ ምን ለብዝበዛ ተዳረገ?
15 አንበሶች በእርሱ ላይ አገሡ፤በኀይለኛ ድምፅም ጮኹበት።ምድሩን ባድማ አድርገውበታል፤ከተሞቹ ተቃጥለዋል፤ ወናም ሆነዋል።
16 ደግሞም የሜምፎስና የጣፍናስ ሰዎች፣መኻል ዐናትሽን ላጩሽ።
17 በመንገድ የሚመራሽን፣ እግዚአብሔር አምላክሽን በመተውሽ፣ይህን በራስሽ ላይ አላመጣሽምን?
18 ከሺሖር ወንዝ ውሃ ለመጠጣት፣አሁንስ ለምን ወደ ግብፅ ወረድሽ?ከኤፍራጥስ ወንዝስ ውሃ ለመጠጣት፣ወደ አሦር መውረድ ለምን አስፈለገሽ?
19 ክፋትሽ ቅጣት ያስከትልብሻል፤ክህደትሽም ተግሣጽ ያመጣብሻል፤ እግዚአብሔር አምላክሽን ስትተዪ፣እኔንም መፍራት ችላ ስትይ፣ምን ያህል ክፉና መራራ እንደሚሆንብሽ፣አስቢ፤ እስቲ አስተውዪ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
20 “ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰበርሁ፤እስራትሽን በጣጠስሁ፤አንቺም፣ ‘አላገለግልህም’ አልሽ፤ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ሥር፣በያንዳንዱም ለምለም ዛፍ ሥር፣ለማመንዘር ተጋደምሽ።
21 እኔ፣ እንደ ምርጥ የወይን ተክል፣ጤናማና አስተማማኝ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ታዲያ ብልሹ የዱር ወይን ተክል ሆነሽ፣እንዴት ተለወጥሽብኝ?
22 በልዩ ቅጠል ብትታጠቢ፣ብዙ ሳሙና ብትጠቀሚም፣የበደልሽ ዕድፍ አሁንም በፊቴ ነው፤”ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
23 “ ‘አልረከስሁም፣በኣሊምን አልተከተልሁም’ እንዴት ትያለሽ?በሸለቆ ውስጥ ምን እንዳደረግሽእስቲ አስቢ፣ምንስ እንደ ፈጸምሽ ተገንዘቢ፤እንደምትፋንን ፈጣን ግመል ሆነሻል፤
24 በምድረ በዳ እንደ ለመደች፣በፍትወቷ ነፋስን እንደምታነፈንፍ፣ የሜዳ አህያ ነሽ፤ከመጎምጀቷ ማን ሊገታት ይችላል?ለሚፈልጓት ሁሉ ያለ ምንም ድካም፤በፍትወቷ ወራት በቀላሉ ትገኝላቸዋለች።
25 እግርሽ እስኪነቃ አትሩጪ፤ጉሮሮሽም በውሃ ጥም እስኪደርቅ አትቅበዝበዢ።አንቺ ግን፣ ‘በከንቱ አትድከም፤ባዕዳን አማልክትን ወድጃለሁ፤እነርሱን እከተላለሁ’ አልሽ።
26 “ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር፣የእስራኤልም ቤት አፍሮአል፤እነርሱ፣ ንጉሦቻቸውና ሹሞቻቸው፣ካህናታቸውና ነቢያታቸው እንዲሁ ያፍራሉ።
27 ዛፉን፣ ‘አንተ አባቴ ነህ’ድንጋዩንም፣ ‘አንተ ወለድኸኝ’ አሉ፤ፊታቸውን ሳይሆን፣ጀርባቸውን ሰጥተውኛልና፤በመከራቸው ጊዜ ግን፣‘መጥተህ አድነን’ ይላሉ።
28 ታዲያ፣ ልታመልካቸው ያበጀሃቸው አማልክት ወዴት ናቸው?በመከራህ ጊዜ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ፣ይሁዳ ሆይ፤ እስቲ ይምጡና ያድኑህ፤የከተሞችህን ቍጥር ያህል፣የአማልክትህም ብዛት እንዲሁ ነውና።
29 “ለምን በእኔ ታማርራላችሁ?ያመፃችሁብኝ እናንተ ሁላችሁ ናችሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።
30 “ልጆቻችሁን በከንቱ ቀጣኋቸው፤እነርሱም አልታረሙም።ሰይፋችሁ እንደ ተራበ አንበሳ፣ነቢያታችሁን በልቶአል።
31 “የዚህ ትውልድ ሰዎች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አስተውሉ፤“እኔ ለእስራኤል ሕዝብ ምድረ በዳ፣ወይስ ድቅድቅ ጨለማ ያለበት ምድር ሆንሁበትን?ሕዝቤ፣ እንደ ልባችን ልንሆን እንፈልጋለን፤ተመልሰንም ወደ አንተ አንመጣም’ ለምን ይላል?
32 ለመሆኑ ቆንጆ ጌጣጌጧን፣ሙሽራ የሰርግ ልብሷን ትረሳለችን?ሕዝቤ ግን፣እጅግ ብዙ ቀን ረስቶኛል።
33 በፍትወት ለማጥመድ እንዴት ስልጡን ነሽ?ልክስክስ ክፉ ሴቶች እንኳ ከመንገድሽ ብዙ ክፋት ይማራሉ።
34 በስርቆት ያልያዝሻቸው፣የንጹሓን ድኾች ደም፣በልብስሽ ላይ ተገኝቶአል።ይህን ሁሉ አድርገሽም፣
35 ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤በእርግጥ ቍጣው ከእኔ ርቆአል’ ትያለሽ።እኔ ግን እፈርድብሻለሁ፤‘ኀጢአት አልሠራሁም ብለሻልና።
36 መንገድሽን እየለዋወጥሽ፣ለምን ትሮጫለሽ?አሦር እንዳዋረደሽ፣ግብፅም እንዲሁ ያዋርድሻል።