1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆርና ሰራዊቱ ሁሉ፣ በግዛቱም ሥር ያሉ መንግሥታትና ሕዝቦች ሁሉ ኢየሩሳሌምንና በአካባቢዋ የሚገኙትን ከተሞች ይወጉ በነበረ ጊዜ፣ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤
2 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ሄደህ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ ልሰጣት ነው፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፤
3 አንተም በእርግጥ ትያዛለህ ዐልፈህም ለእርሱ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም። የባቢሎንን ንጉሥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።
4 “ ‘ነገር ግን፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፤ በሰይፍ አትሞትም፤
5 በሰላም ትሞታለህ። ሕዝቡ ከአንተ በፊት ለነበሩት ነገሥታት አባቶችህ ክብር በቀብራቸው ጊዜ እሳት እንዳነደዱ፣ በቀብርህም ጊዜ ስለ ክብርህ እሳት ያነዳሉ፤ “ዋይ ዋይ ጌታችን!” እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ ራሴ ይህን ቃል ተናግሬአለሁና፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”
6 ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤
7 በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩና።
8 ንጉሡ ሴዴቅያስ ባሪያዎችን ነጻ ለማውጣት ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።
9 እያንዳንዱ ሰው፣ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባሪያውን ነጻ ማውጣት ነበረበት፤ ማንም ሰው አይሁዳዊ ወንድሙን በባርነት መግዛት አልነበረበትም።
10 በዚህ ቃል ኪዳን የተስማሙት ባለሥልጣኖችና ሕዝቡ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና ከእንግዲህ ባሪያ አድርገው ላይገዟቸው ተስማሙ።
11 በኋላ ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ነጻ የለቀቋቸው ባሪያዎቻቸውን እንዲመለሱ አደረጓቸው፤ እንደ ገናም ባሪያ አድርገው ገዟቸው።
12 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
13 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በባርነት ከተገዙበት ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻችሁ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፤
14 ‘ራሱን በባርነት ለእናንተ የሸጠውን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ በየሰባት ዓመቱ ነጻ ትለቃላችሁ፤ ስድስት ዓመት ከተገዛላችሁ በኋላ ነጻ ታወጡታላችሁ።’ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም።
15 እናንተም አሁን ንስሓ በመግባት በፊቴ ትክክለኛ ነገር አደረጋችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ለወገኖቻችሁ ነጻነት ዐወጃችሁ፤ ስሜ በሚጠራበት ቤትም በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ።
16 ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አረከሳችሁ፤ ወደ ፈለጉበት እንዲሄዱ ነጻ የለቀቃችኋቸውንም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻችሁን መለሳችሁ፤ እንደ ገናም ባሪያዎቻችሁ አደረጋችኋቸው።
17 “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ለወንድሞቻችሁና ለወገኖቻችሁ ነጻነት አላወጃችሁምና አልታዘዛችሁኝም። እንግዲህ እኔ ‘ነጻነት’ ዐውጅላችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። ይኸውም በሰይፍ፣ በቸነፈርና በራብ የምትወድቁበት ‘ነጻነት’ ነው። ለምድር መንግሥታት ሁሉ መሠቀቂያ አደርጋችኋለሁ።
18 ኪዳኔን ያፈረሱትንና በፊቴ የገቡትን የኪዳኑን ቃል ያልፈጸሙትን ሰዎች ሥጋውን ሁለት ቦታ ከፍለው በመካከሉ እንዳለፉት፣ እንደ እንቦሳው አደርጋቸዋለሁ።
19 የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን መሪዎች፣ የቤተ መንግሥቱን ባለሟሎች፣ ካህናቱንና በእንቦሳው ሥጋ መካከል ያለፉትን ሕዝብ ሁሉ፣
20 ነፍሳቸውን ለሚሹ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።
21 “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን፣ ነፍሳቸውን ለሚሹ ጠላቶቻቸው ይኸውም ለጊዜው እናንተን ከመውጋት ለተመለሱ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት አሳልፌ እሰጣለሁ።
22 እነሆ፤ አዛቸዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደዚህችም ከተማ እንደ ገና እመልሳቸዋለሁ። እነርሱም ይወጓታል፤ ይይዟታል፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው፣ ባድማ አደርጋቸዋለሁ።