1 “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣ወደ እርሷ ይመለሳልን?ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን?አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋር አመንዝረሻል፤ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?”ይላል እግዚአብሔር።
2 “እስቲ ቀና ብለሽ ጭር ያሉትን ኰረብቶች ተመልከቺ፣በርኵሰት ያልተጋደምሽበት ቦታ ይገኛልን?በበረሓ፣ እንደ ተቀመጠ ዘላን ዐረብ፣በየመንገዱ ዳር ተቀምጠሽ ወዳጆችሽን ጠበቅሽ።በዝሙትሽና በክፋትሽ፣ምድሪቱን አረከስሽ።
3 ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፤ኋለኛው ዝናብም ጠፋ።አንቺ ግን አሁንም የጋለሞታ ገጽታ አለብሽ፤ዐይንሽን በዕፍረት አልሰብር ብለሻል።
4 አሁንም ወደ እኔ ተጣርተሽ፣‘አባቴ፣ የልጅነት ወዳጄ፣
5 ሁል ጊዜ ትቈጣለህን?ቍጣህስ ለዘላለም ነውን?’ አላልሽኝም?የምትናገሪው እንዲህ ነው፤ይሁን እንጂ የቻልሽውን ክፋት ሁሉ ታደርጊያለሽ።”
6 እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፤ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ከፍ ወዳለው ኰረብታ ሁሉ ወጥታ፣ ወደ ለመለመው ዛፍ ሥር ሁሉ ሄዳ በዚያ አመነዘረች።
7 ይህን ሁሉ ካደረገች በኋላ፣ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ሆኖም አልተመለሰችም፤ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አየች።
8 ለከዳተኛ ዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች።
9 በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች፤
10 ይህም ሁሉ ሆኖ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳ ወደ እኔ የተመለሰችው በማስመሰል እንጂ በሙሉ ልቧ አልነበረም” ይላል እግዚአብሔር።
11 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ከከሓዲዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ጻድቅ ሆና ተገኘች።
12 ሂድና ይህን መልእክት ወደ ሰሜን እንዲህ ብለህ ተናገር፤“ ‘ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፤‘እኔ መሓሪ ስለ ሆንሁ፣ከእንግዲህ በቍጣ ዐይን አላይሽም’ይላል እግዚአብሔር። ‘ለዘላለም አልቈጣም።
13 በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅሽ፣ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣በየለምለሙ ዛፍ ሥር አሳልፈሽ በመስጠት፣ለእኔ ባለመታዘዝሽ፣በደለኛ መሆንሽን ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ’ ”ይላል እግዚአብሔር።
14 “ከዳተኛ ልጆች ሆይ፤ እኔ ባለቤታችሁ ነኝና ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከአንድ ከተማ አንድ፣ ከአንድ ነገድ ሁለት መርጫችሁ ወደ ጽዮን አመጣችኋለሁ።
15 እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ።
16 ቍጥራችሁ በምድሪቱ እጅግ በሚበዛበት ጊዜም ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ዘመን፣ ‘የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት’ ብለው ከእንግዲህ አይጠሩም፤ ትዝ አይላቸውም፤ አያስታውሱትምም፤ አይጠፋም፤ ሌላም አይሠራም።
17 በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን፣ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ብለው ይጠሯታል፤ መንግሥታትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ የክፉ ልባቸውንም እልኸኝነት ከእንግዲህ አይከተሉም።
18 በዚያን ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።
19 “እኔም፣“ ‘የተመረጠችውን ምድር፣የትኛውም ሕዝብ ያላገኘውን የተዋበች ርስት ልሰጥሽ፣እንደ ወንዶች ልጆቼ ምንኛ በደስታ ልቍጠርሽ” አልሁ፤‘አባቴ’ ብለሽ የምትጠሪኝ፣እኔንም ከመከተል ዘወር የማትይ መስሎኝ ነበር።
20 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለባሏ ታማኝ እንዳልሆነች ሚስት፣ስታታልሉኝ ኖራችኋል፤”ይላል እግዚአብሔር።
21 እግዚአብሔር አምላካቸውን በመርሳት፣መንገዳቸውን አጣመዋልና፣የእስራኤል ሕዝብ ጩኸት፣አሳዛኝ ልቅሶ ባድማ ከሆኑት ኰረብታዎች ተሰማ።
22 “እናንት ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ፤ከዳተኝነታችሁን እፈውሳለሁ።”“አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና፤አዎን፤ ወደ አንተ እንመጣለን።
23 በእርግጥ በኰረብቶች ላይ፣እንዲሁም በተራሮች ላይ፣ ሆ! ብለን መውጣታችን መታለል ነው፤በእርግጥ የእስራኤል መዳን፣በአምላካችን በእግዚአብሔር ነው።
24 ከለጋ ዕድሜአችን ጀምሮ፣የአባቶቻችንን የድካም ፍሬዎች፣በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን፣ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን፣ ነውረኛ ጣዖቶች በሏቸው።