ኤርምያስ 32:6-12 NASV

6 ኤርምያስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ አለ፦

7 “የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ ‘የመቤዠት መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በዓናቶት ያለውን መሬቴን ግዛኝ’ ይልሃል።”

8 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ዐወቅሁ፤

9 ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብር መዝኜ ሰጠሁት።

10 በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።

11 የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤

12 በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።