1 ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ በግዞት ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እርሱ መጣ፦
2 “ምድርን የፈጠራት፣ ያበጃትና የመሠረታት እግዚአብሔር፣ ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፣ እርሱ እንዲህ ይላል፤
3 ‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ፤’
4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከባቢሎናውያን ጋር ባለው ውጊያ፣ ዐፈር በመደልደልና በሰይፍ የሚደረገውን ጥቃት ለመከላከል ስለ ፈረሱት ስለዚህች ከተማ ቤቶችና ስለ ይሁዳ ነገሥታት ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤