1 ኢየሩሳሌም የተያዘችው እንዲህ ነበር፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አሰልፎ በመምጣት ኢየሩሳሌምን ከበባት።
2 በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ አንደኛው ዓመት በአራተኛው ወር፣ በወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማዪቱ ቅጥር ተሰበረ።
3 የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ፦ የሳምጋሩ ኤርጌል ሳራስር፣ ዋና አዛዡ ናቦሠርሰኪም፣ ከፍተኛው ሹም ኤርጌል ሳራሳር እንዲሁም ሌሎቹ የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ ገብተው በመካከለኛው በር ተቀመጡ።
4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ እነርሱን ባዩ ጊዜ ሸሹ፤ በሌሊት በንጉሡ አትክልት ስፍራ በኩል አድርገው በሁለቱ ቅጥር መካከል ከከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።