1 የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን ኤርምያስን ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ወደ ባቢሎን በሚወስዱት ምርኮኞች ሁሉ መካከል በራማ በሰንሰለት ታስሮ ባገኘው ጊዜ አስፈታው፤ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።
2 የዘበኞቹ አዛዥ ኤርምያስን ለብቻው ወስዶ፣ እንዲህ አለው፤ “አምላክህ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ይህን ጥፋት ተናገረ፤
3 አሁንም እግዚአብሔር አመጣው፤ እንደ ተናገረውም አደረገ። ይህ ሁሉ የሆነው እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና እርሱን ስላልታዘዛችሁ ነው።
4 እነሆ፤ ዛሬ የእጅህን ሰንሰለት ፈታሁልህ። ከፈለግህ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎንና፤ እኔም እንከባ ከብሃለሁ፤ ካልፈለግህ ግን አትምጣ። እነሆ፤ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ደስ ወዳሰኘህ ሂድ።”
5 ኤርምያስ ገና መልስ ሳይሰጥ ናቡዘረዳን በመቀጠል፣ “የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፤ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ደስ ወዳሰኘህ ስፍራ ሂድ” አለው። የዘበኞቹ አዛዥ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው፤