ሕዝቅኤል 13:10-16 NASV

10 “ሰላም ሳይኖር፣ ‘ሰላም አለ’ እያሉ ሕዝቤን ያስታሉ፤ ሕዝቡ ካብ ሲሠራ እነርሱ በኖራ ይለስናሉ፤

11 ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል።

12 እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ ‘የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?’ ብለው አይጠይቋችሁምን?”

13 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል።

14 በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

15 መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤

16 ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”