ሕዝቅኤል 13:11-17 NASV

11 ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል።

12 እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ ‘የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?’ ብለው አይጠይቋችሁምን?”

13 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል።

14 በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

15 መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤

16 ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

17 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ከራሳቸው አመንጭተው ትንቢት ወደሚናገሩ ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን መልስ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤