ሕዝቅኤል 16:39-45 NASV

39 ለወዳጆችሽ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም ጒብታሽንና የማምለኪያ ኰረብታሽን ያፈርሳሉ፤ ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽን ይቀሙሻል፤ ዕርቃንሽንና ባዶ እጅሽን ያስቀሩሻል።

40 ሕዝብ ያነሣሡብሻል፤ በድንጋይ ይወግሩሻል፤ በሰይፍ ይቈራርጡሻል፤

41 ቤቶችሽን ያቃጥላሉ፤ በብዙ ሴቶችም ፊት ቅጣት ያመጡብሻል። ግልሙትናሽን አስተውሻለሁ፤ ከእንግዲህም ለወዳጆችሽ ዋጋ አትከፍዪም።

42 በዚህም በአንቺ ላይ የነበረው ቍጣዬ ይበርዳል፤ የቅናቴ ቍጣም ከአንቺ ይርቃል። እኔም ዝም እላለሁ፤ ከእንግዲህም አልቈጣም።

43 “ ‘በእነዚህ ነገሮች አስቈጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላሰብሽም፤ ስለዚህ የሥራሽን እከፍልሻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በሌላው አስጸያፊ ተግባርሽ ሁሉ ላይ ዘማዊነትን አልጨመርሽምን?

44 “ ‘በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፣ “ሴት ልጅ በእናቷ ትወጣለች” እያለ ይመስልብሻል።

45 አንቺ ባሏንና ልጆቿን የምትጸየፍ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚጸየፉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ። እናታችሁ ኬጢያዊት፣ አባታችሁም አሞራዊ ነበሩ።