2 “ስለ እስራኤል ምድር፣“ ‘አባቶች ጐምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤የልጆችንም ጥርስ አጠረሰ’ እያላችሁ የምትመስሉት ተምሳሌት ምን ለማለት ነው?
3 “በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ ከእንግዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ምድር አትመስሉም።
4 እነሆ ነፍስ ሁሉ የእኔ ናት፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች ሁሉ የልጁም ነፍስ የእኔ ናት፤ ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።
5 “በቅንነትና በትክክል የሚሠራ፣ጻድቅ ሰው ቢገኝ፣
6 በኰረብታ ባሉ አብያተ ጣዖት የቀረበውን አይበላም፤በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት አይመለከትምየባልንጀራውን ሚስት አያባልግም፤ከሴት ጋር በወር አበባዋ ጊዜ አይተኛም።
7 ማንንም አይጨቍንም፤ነገር ግን በመያዣ የወሰደውን እንኳ ለተበዳሪው ይመልሳል፤ለተራበ የራሱን እንጀራ፣ለተራቈተም ልብስ ይሰጣል እንጂ፣በጒልበት አይቀማም።
8 በዐራጣ አያበድርም፣ከፍተኛ ወለድም አይቀበልም።እጁን ከበደል ይሰበስባል፤በሰውና በሰው መካከል በትክክል ይፈርዳል።