1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ አትፈርድባትምን? ደም በምታፈሰው በዚህች ከተማ ላይ አትፈርድባትምን? ጸያፍ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤
3 እንዲህም በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመካከልሽ ደምን በማፍሰስና ጣዖታትን በመሥራት ራስሽን የምታረክሺ፣ ፍርድንም በራስሽ ላይ የምታፈጥኚ ከተማ ሆይ፤
4 ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ በሠራሽውም ጣዖት ረክሰሻል፤ ከዚህም የተነሣ ቀንሽን አቅርበሻል፤ ዕድሜሽንም አሳጥረሻል። ስለዚህ ለአሕዛብ መዘባበቻ፣ ለአገሩም ሁሉ መሣለቂያ አደርግሻለሁ።