ሕዝቅኤል 22:19-25 NASV

19 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ሁላችሁም የብረት ዝቃጭ ስለ ሆናችሁ ወደ ኢየሩሳሌም እሰበስባችኋለሁ።

20 ሰው ብርንና መዳብን፣ ብረትንና እርሳስን እንዲሁም ቈርቈሮን ለማቅለጥ በከውር ውስጥ አስገብቶ እሳት እንደሚያነድበት፣ እኔም እንደዚሁ በቍጣዬና በመዓቴ ወደ ከተማዪቱ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም አቀልጣችኋለሁ።

21 ሰብስቤአችሁ የቍጣዬን እሳት በእስትንፋሴ አነድባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያ ውስጥ ቀልጣችሁ ትቀራላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።

22 ብር በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፣ እናንተም በከተማዋ ውስጥ ትቀልጣላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።’ ”

23 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምድሪቱን፣ ‘አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት።

25 መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ።