ሕዝቅኤል 23:24-30 NASV

24 እነርሱም የጦር መሣሪያ፣ ሠረገላና ጋሪ በመያዝ ብዙ ሕዝብ ሆነው ይመጡብሻል፤ ትላልቅና መለስተኛ ጋሻ በማንገብና የራስ ቍር በመድፋት በየአቅጣጫው ይሰለፉብሻል፤ እኔም ለፍርድ በእጃቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ በሕጋቸውም መሠረት ይቀጡሻል።

25 የቅናት ቍጣዬን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ እነርሱም በአንቺ ላይ በቍጣ ይወጣሉ፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንቺ ወገን የተረፉትም በሰይፍ ይወድቃሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዱብሻል፤ የተረፉትንም እሳት ይበላቸዋል።

26 ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽንም ይወስዱብሻል።

27 በግብፅ የጀመርሽውን ብልግናና ሴሰኝነት ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ አንቺም ዐይንሽን ወደ እነዚህ አታነሺም፤ ከእንግዲህ ግብፅን አታስቢም።

28 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ ተጸይፈሻቸው ከእነርሱ ዘወር ላልሽው ለጠላሻቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ።

29 እነርሱም በጥላቻ ይቀርቡሻል፤ የለፋሽበትንም ሁሉ ይቀሙሻል፤ ከማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ያስቀሩሻል፤ የሴሰኝነትሽ ኀፍረት ይገለጣል። ብልግናሽና ገደብ የለሽ ርኵሰትሽ፣

30 ይህን አምጥተውብሻል፤ ከአሕዛብ ጋር በማመንዘር በጣዖቶቻቸው ረክሰሻልና።