1 በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቍጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፤“ ‘በክብር ከአንተ ጋር ማን ሊወዳደር ይችላል፤
3 ለጫካው ጥላ የሆኑ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች የነበሩትን፣እጅግ መለሎ ሆኖ፣ጫፉ ሰማይ የደረሰውን፣የሊባኖስን ዝግባ አሦርን ተመልከት።
4 ውሆች አበቀሉት፤ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣መስኖዎቻቸውን ለቀቁት።
5 ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣እጅግ ከፍ አለ፤ቅርንጫፎቹ በዙ፤ቀንበጦቹ ረዘሙ፤ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።
6 የሰማይ ወፎች ሁሉ፣በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጆአቸውን ሠሩ፤የምድር አራዊት ሁሉ፣ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ።ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣ከጥላው ሥር ኖሩ።
7 ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋር፣ውበቱ ግሩም ነበር፤ብዙ ውሃ ወዳለበት፣ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።