ሕዝቅኤል 33:11-17 NASV

11 እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’

12 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’

13 ጻድቁን ሰው በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከጽድቅ ሥራው አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል።

14 እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀና የሆነውንና ትክክለኛውንም ነገር ቢያደርግ፣

15 ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዛት ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በእርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም።

16 ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።

17 “ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው።