15 ከእንግዲህ የሕዝቦችን ዘለፋ እንድትሰሙ አላደርግም፤ በሰዎችም ስድብ አትሠቃዩም፤ ከእንግዲህ ለሕዝባችሁ መሰናክል አትሆኑም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
16 እንደ ገና የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
17 የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ሕዝብ በገዛ ምድራቸው ይኖሩ በነበረበት ጊዜ በሥራቸውና በአኗኗራቸው አረከሷት፤ ጠባያቸውም በፊቴ፣ ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ዐይነት ነበር።
18 ስለዚህ በምድሪቱ ላይ ደም ስላፈሰሱና በጣዖታቶቻቸው ስላረከሷት፣ መዓቴን አፈሰ ስሁባቸው።
19 በአሕዛብ መካከል በተንኋቸው፤ እነርሱም በየአገሩ ተበታተኑ፤ እንደ ጠባያቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው።
20 በአሕዛብ መካከል በሄዱበት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለ እነርሱ፣ ‘እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ናቸው፤ ዳሩ ግን የእርሱን ምድር ትተው እንዲሄዱ ተገደዱ’ ተብሎአልና።
21 የእስራኤል ቤት በሄዱበት በአሕዛብ መካከል ሁሉ፣ ስላረከሱት ቅዱስ ስሜ ገዶኛል።