ሕዝቅኤል 36:8-14 NASV

8 “ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ግን፤ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቅርንጫፍ ታወጣላችሁ፤ ፍሬም ታፈራላችሁ፤ በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉና።

9 ስለ እናንተ ይገደኛል፤ በበጎነትም እመለከታችኋለሁ፤ ትታረሳላችሁ፤ ዘርም ይዘራባችኋል።

10 መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ።

11 በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

12 ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።

13 “ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቡ እናንተን፣ ‘ሰዎችን ቦጫጭቀው ይበላሉ፤ ሕዝብንም ልጅ አልባ ያደርጋሉ’ ስላሏችሁ፣

14 ከእንግዲህ ሰው አትበሉም፤ ሕዝቡንም ልጅ አልባ አታደርጉትም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።