ሕዝቅኤል 40:5-11 NASV

5 የቤተ መቅደሱን ዙሪያ ሙሉ በሙሉ የከበበ ቅጥር አየሁ፤ በሰውየውም እጅ ርዝመቱ ስድስት ክንድ የሆነ መለኪያ ዘንግ አየሁ፤ እያንዳንዱ ክንድ፣ አንድ ክንድ ከስንዝር ነበር፤ እርሱም ቅጥሩን ለካው፤ ስፋቱ አንድ መለኪያ ዘንግ ሲሆን፣ ቁመቱም እንዲሁ አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር።

6 ከዚያም በምሥራቅ ትይዩ ወዳለው በር መጣ፤ ደረጃዎቹን ወጥቶ የበሩን መግቢያ መድረክ ለካ፤ ቍመቱም አንድ ዘንግ ነበር።

7 የዘብ ጠባቂ ቤቶች፣ ቁመታቸው አንድ መለኪያ ዘንግ፣ ወርዳቸውም አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር፤ በቤቶቹም መካከል ያሉት ግንቦች ውፍረት አምስት ክንድ ነበር። ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ባለው መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ በውስጥ በኩል ያለው የበሩ መድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበር።

8 ከዚያም የመግቢያውን በር መተላለፊያውን በረንዳ ለካ፤

9 ቍመቱ ስምንት ክንድ፣ የዐምዶቹም ውፍረት ሁለት ክንድ ነበር። የመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳ፣ ከቤተ መቅደሱ ትይዩ ነው።

10 በምሥራቁ በር ግራና ቀኝ መጠናቸው እኩል የሆነ ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች ነበሩ፤በመካከላቸው ወጣ ወጣ ብለው የሚታዩትም ግንቦች ተመሳሳይና እኩል ነበሩ።

11 ከዚያም የበሩን ስፋት ለካ፤ ወርዱ ዐሥር ክንድ፣ ርዝመቱም ዐሥራ ሦስት ክንድ ነበር።