ሕዝቅኤል 43:6-12 NASV

6 ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ሳለ፣ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲናገረኝ ሰማሁ፤

7 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።

8 በእኔና በጣዖታቱ መካከል ግንብ ብቻ ሲቀር፣ መድረኮቻቸውን ከመድረኬ አጠገብ፣ መቃኖቻቸውን ከመቃኖቼ አጠገብ በማድረግ፣ በአስጸያፊ ድርጊታቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።

9 ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።

10 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ኀጢአታቸው ያፍሩ ዘንድ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ቤተ መቅደሱን አሳያቸው፤ ንድፉንም ያስተውሉ፤

11 ስላደረጉት ነገር ሁሉ ኀፍረት የሚሰማቸው ከሆነ፣ የቤተ መቅደሱን ንድፍ እንዲያውቁት አድርግ፤ ይኸውም አሠራሩን፣ መውጫና መግቢያውን፣ አጠቃላይ ንድፉን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ነው። ንድፉንና ሥርዐቱን እንዲጠብቁና እንዲከተሉ እነዚህን ሁሉ እነርሱ ባሉበት ጻፋቸው።

12 “የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ አካባቢ ያለው ስፍራ ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የቤተ መቅደሱም ሕግ ይኸው ነው።