13 ‘ “የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆመር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆመር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው።
14 ዘይቱ በባዶስ ሲለካ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆመር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆመር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆመር ጋር እኩል ነውና።
15 እንዲሁም ውሃ ከጠገበው ከእስራኤል መሰማሪያ፣ ሁለት መቶ በግ ካለው ከእያንዳንዱ መንጋ አንድ በግ ይውሰድ። ይህ ሁሉ ለሕዝቡ ማስተስረያ ለሚሆነው ለእህል ቍርባን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ይውላል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህን ልዩ መባ ለእስራኤል ገዥ ይሰጣሉ።
17 በበዓላት፣ በወር መባቻና በሰንበታት፣ ለእስራኤል ቤት በተወሰኑት በዓላት ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ማቅረብ የገዡ ኀላፊነት ነው፤ ለእስራኤል ቤት ማስተስረያ እንዲሆንም የኀጢአት መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርባል።’
18 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፤ መቅደሱንም አንጻው።
19 ካህኑም ከኀጢአቱ መሥዋዕት ደም በመውሰድ በቤተ መቅደሱ በር መቃኖች፣ በመሠዊያው ላይኛ ዕርከን አራት ማእዘንና በውስጠኛው አደባባይ በር መቃኖች ላይ ይርጨው።