ሕዝቅኤል 47:12-18 NASV

12 በወንዙም ዳርና ዳር፣ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶች ሁሉ ይበቅላሉ፤ ቅጠላቸው አይደርቅም፤ ፍሬ አልባም አይሆኑም። ከመቅደሱ የሚወጣው ውሃ ስለሚፈስላቸው በየወሩ ያፈራሉ፤ ፍሬያቸው ለምግብ፣ ቅጠላቸውም ለፈውስ ይሆናል።

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ የምታከፋፍሉባቸው፣ ወሰኖች እነዚህ ናቸው፤ ዮሴፍ ሁለት ዕጣ ይኑረው።

14 እኩል አድርጋችሁ ከፋፍሉት፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ በተዘረጋች እጅ ስለ ማልሁ፣ ምድሪቱ ርስታችሁ ትሆናለች።

15 “የምድሪቱ ወሰን ይህ ነው፤“በሰሜን በኩል ከታላቁ ባሕር አንሥቶ በሔትሎን መንገድ በሐማት መተላለፊያ አድርጎ እስከ ጽዳድ ይደርሳል፤

16 ከዚያም ቤሮታን፣ በደማስቆና በሐማት ወሰን መካከል ያለውን ሲብራይምን ዐልፎ፣ በሐውራን ወሰን ላይ እስካለው እስከ ሐጸርሃቲኮን ይዘልቃል።

17 ወሰኑ ከባሕሩ በመነሣት፣ በሰሜኑ የደማስቆ ድንበር አድርጎ፣ የሐማትንም ዳርቻ ወደ ሰሜን ትቶ እስከ ሐጸርዔናን ይዘልቃል።

18 “በምሥራቅ በኩል ወሰኑ በሐውራንና በደማስቆ መካከል፣ በገለዓድና በእስራኤል ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል፤ የምሥራቁ ድንበር እስከ ምሥራቁ ባሕር ይወርድና እስከ ታማር ይዘልቃል፤ ይህም የምሥራቁ ወሰን ይሆናል።