ኢሳይያስ 1:1-7 NASV

1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፣ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፤

2 ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናግሮአልና፤“ልጆች ወለድሁ፣ አሳደግኋቸውም፤እነርሱ ግን ዐመፁብኝ።

3 በሬ ጌታውን፣አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤እስራኤል ግን አላወቀም፤ሕዝቤም አላስተዋለም።”

4 እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣በደል የሞላበት ወገን፣የክፉ አድራጊ ዘር፣ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ እግዚአብሔርን ትተዋል፤የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል።

5 ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ?ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ?ራሳችሁ በሙሉ ታሞአል፤ልባችሁ ሁሉ ታውኮአል።

6 ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጒራችሁጤና የላችሁም፤ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤አልታጠበም፤ አልታሰረም፤በዘይትም አልለዘበም።

7 አገራችሁ ባድማ፣ከተሞቻችሁ በእሳት የተቃጠሉ ይሆናሉ፤ዐይናችሁ እያየ፣መሬታችሁ በባዕድ ይነጠቃል፤ጠፍም ይሆናል።