ኢሳይያስ 10:12-18 NASV

12 ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፣ እንዲህ ይላል የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤

13 የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤“ ‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና።የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ።

14 ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፣እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤ሰዎች የተተወ ዕንቍላል እንደሚሰበስቡ፣እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ክንፉን ያራገበ የለም፤አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’ ”

15 መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይኵራራልን?መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን?በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፣ዘንግም ራሱን ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኵራራ ነው።

16 ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳትይለኰሳል።

17 የእስራኤል ብርሃን እሳት፣ቅዱሱም ነበልባል ይሆናል፤በአንድ ቀንምእሾኹንና ኵርንችቱን እሳት ይበላዋል፤

18 ሕመምተኛ እየመነመነ እንደሚሞት፣የደኑን ክብርና የለማውን ዕርሻ፣ነፍስና ሥጋንም ፈጽሞ ያጠፋል።