6 ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።
7 ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ፤አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል።
8 ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጒድጓድ ላይ ይጫወታል፤ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጒድጓድ ይከትታል።
9 በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጒዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅትሞላለችና።
10 በዚያን ቀን፣ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ መንግሥታት ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል።
11 በዚያን ቀን፣ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደ ገና የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር፣ ከታችኛው ግብፅ፣ ከላይኛው ግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤላም፣ ከባቢሎን፣ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል።
12 ለመንግሥታት ምልክትን ያቆማል፤ከእስራኤልም የተሰደዱትን መልሶ ያመጣቸዋል፤የተበተኑትን የይሁዳ ሕዝብ፣ከአራቱ የምድር ማእዘን ይሰበስባል።