10 ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤እልልታም ቀርቶአል።በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና።
11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጒርጒሮ ታሰማለች፤አንጀቴም ስለ ቄርሔሬስ ታለቅሳለች፤
12 ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣ዋጋ የለውም።
13 እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14 አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የሞዓብ ክብርና የሕዝቧ ብዛት በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚቀረውም ሕዝብ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”