6 እናንት በደሴቲቱ የምትኖሩ፣ በዋይታ አልቅሱ፤ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤
7 እግሮቿ ሩቅ አገር የወሰዷት፣በዚያም እንድትሰፍር ያደረጓት፣ጥንታዊቷ የድሮ ከተማ፣የተድላ የደስ ከተማችሁ ይህች ናትን?
8 አክሊል በምታቀዳጀዋ፣ነጋዴዎቿ መሳፍንት በሆኑ፣በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፣በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር?
9 የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊያዋርድ፣በምድር ከፍ ከፍ ያለውንም ሁሉ ዝቅ ሊያደርግ፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖአል።
10 የተርሴስ ልጅ ሆይ፤ከእንግዲህ የሚከለክልሽ የለምናእንደ ዐባይ ወንዝ ምድርሽን አጥለቅልቂ።
11 እግዚአብሔር እጁን በባሕር ላይ ዘረጋ፤መንግሥታቷንም አስደነገጠ፤የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ፣ትእዛዝ ሰጠ፤
12 እንዲህም አለ፤ “አንቺ የተቀጠቀጥሽ የሲዶን ድንግል ሆይ!ከእንግዲህ ደስ አይበልሽ፤“ተነሺ ወደ ቆጵሮስ ተሻገሪ፤በዚያም እንኳ ሰላም አታገኚም።”