ኢሳይያስ 29:8-14 NASV

8 የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ፣ነገር ግን ሲነቃ ራቡ እንዳልለቀቀው፣የጠማውም ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ፣ነገር ግን ሲነቃ እንደ ዛለና ጥማቱም እንዳልተወው፣የጽዮንን ተራራ የሚወጋ፣የአሕዛብ መንጋ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።

9 ነሁሉሉ፤ ተደነቁም፤ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።

10 እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ጥሎባችኋል፤ዐይኖቻችሁን፣ ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤ራሶቻችሁን፣ ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።

11 ይህ ሁሉ ራእይ በጥቅልል መጽሐፍ ውስጥ እንደ ታሸገ ቃል ሆኖባችኋል። ጥቅልሉንም መጽሐፍ ማንበብ ለሚችል ሰው፣ “እባክህ አንብልን” ብላችሁ ብትሰጡት፣ “ታሽጓልና አልችልም” ይላችኋል።

12 ደግሞም ጥቅልሉን መጽሐፍ ማንበብ ለማይችል ሰው፣ “እባክህን አንብልን” ብላችሁ ብትሰጡ፣ “ማንበብ አልችልም” ይላችኋል።

13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤በከንፈሩም ያከብረኛል፤ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤የሚያመልከኝም፣ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው።

14 ስለዚህ ይህን ሕዝብ በድንቅ ላይ ድንቅነገር እያደረግሁ፣ዳግመኛ አስገርመዋለሁ፤የጥበበኞች ጥበብ ይጠፋል፤የአስተዋዮችም ማስተዋል ይበናል።”