ኢሳይያስ 30:13-19 NASV

13 ስለዚህ ይህ ኀጢአት፣ተሰነጣጥቆ ሊወድቅ እንደ ደረሰ፣ሳይታሰብ ድንገት እንደሚወድቅ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።

14 ከስብርባሪዎቹም መካከል፣ለፍም መጫሪያ፣ለውሃ መጥለቂያ ገል እስከማይገኝ ድረስ፣ምንም ሳይቀር ክፉኛ እንደሚንኰታኰት፣የሸክላ ዕቃ ይደቃል።”

15 የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤

16 ደግሞም ‘አይሆንም፣ በፈረስ እንሸሻለን’ አላችሁ፤ስለዚህ ትሸሻላችሁ።ደግሞም፣ ‘በፈጣን ፈረስ እናመልጣለን’ አላችሁ፤ስለዚህ አሳዳጆቻችሁም ፈጣን ይሆናሉ።

17 በተራራ ዐናት ላይ እንደ ተተከለ ሰንደቅ ዐላማ፣በኰረብታም ላይ እንደ ቆመ ምልክት፣ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስበአንድ ሰው ዛቻ፣ሺህ ሰው ይሸሻል፤በአምስት ሰው፣ሁላችሁ ትሸሻላችሁ።”

18 እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት የተባረኩ ናቸው።

19 በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ ጩኸትህን እንደሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል።