ኢሳይያስ 36:1-7 NASV

1 ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው።

2 የአሦርም ንጉሥ የጦር አዛዡን ከብዙ ሰራዊት ጋር ከለኪሶ፣ ንጉሡ ሕዝቅያስ ወዳለበት፣ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። የጦር አዛዡም ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ፣ በላይኛው ኵሬ ቦይ አጠገብ ደርሶ ቆመ፤

3 የቤተ መንግሥቱ አስተዳዳሪ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።

4 የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤“ ‘ታላቁ ንጉሥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው?

5 የጦር ስልትና ጠንካራ ሰራዊት አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ፍሬ ቢስ ቃል ብቻ ትናገራለህ። ለመሆኑ፣ በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?

6 እነሆ፤ ሰው ሲመረ ኰዘው እጅ ወግቶ በሚያቈስለው፣ በተሰነጠቀ ሸምበቆ በግብፅ ተማምነሃል፤ የግብፅ ንጉሥ፣ ፈርዖንም ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።

7 ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የእርሱንማ ማምለኪያ ኰረብቶችና መሠዊያዎች ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ እንዲህ ባለው በአንዱ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን?