ኢሳይያስ 36:10-16 NASV

10 ደግሞስ ይህን ምድር ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህ አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋው ነግሮኛል።’ ”

11 ኤልያቄምና ሳምናስ እንዲሁም ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እባክህ በምናውቀው በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚያውቀው በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት።

12 ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ነገሮች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኩስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው።

13 የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ቋንቋ በታላቅ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።

14 ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ እርሱ ሊያድናችሁም አይችልም።

15 “እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር አትሰጥም’ እያለ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።’

16 “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ከእኔ ጋር ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤