ኢሳይያስ 36:16-22 NASV

16 “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ከእኔ ጋር ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤

17 ይኸውም መጥቼ የእህልና የአዲስ ወይን ጠጅ ምድር ወደሆነችው፣ የእንጀራና የወይን ምድር ወደሆነችው፣ ምድራችሁን ወደ ምትመስል አገር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።’

18 “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ያድነናል’ በማለት አያታልላችሁ”፤ ለመሆኑ፣ እስካሁን ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያዳነ የየትኛው ሕዝብ አምላክ ነው።

19 የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክትስ የት አሉ? እነዚህ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?

20 ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ፣ ምድሩን ከእጄ ለማዳን የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ፣ እግዚአብሔር እንዴት ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያድን ይችላል?”

21 ሕዝቡ ግን ንጉሡ፣ “መልስ አትስጡት” ብሎ አዞ ስለ ነበር፣ ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም።

22 የቤተ መንግሥት አስተዳዳሪ የነበረው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የጦር አዛዡ የተናገረውንም ሁሉ ነገሩት።