ኢሳይያስ 47:10-15 NASV

10 በክፋትሽ ተማምነሽ፣‘ማንም አያየኝም’ አልሽ፤ደግሞም፣ ‘እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ የለም’ባልሽ ጊዜ፣ጥበብሽና ዕውቀትሽ አሳሳቱሽ።

11 ጥፋት ይመጣብሻል፤ነገር ግን በአስማትሽ እንዴት እንደም ታርቂው አታውቂም፤ወጆ ከፍለሽ ለማስወገድ የማትችዪው፣ጒዳት ይወድቅብሻል፤ያላሰብሽው አደጋ፣ድንገት ይደርስብሻል።

12 በይ እንግዲህ፣ “ከልጅነትሽ ጀምሮ የደከምሽባቸውን፣አስማቶችሽን፣ብዙ መተቶችን ቀጥዪባቸው፤ምናልባት ይሳካልሽ፤ምናልባትም ጠላቶችሽን ታሸብሪባቸው ይሆናል።

13 የተቀበልሽው ምክር ሁሉ ድካም ብቻ ሆኖ አስቀርቶሻል፤እነዚያ ከወር እስከ ወር ከዋክብትን አንጋጦ በማየት የሚተነብዩ፣ኮከብ ቈጣሪዎች እስቲ ይምጡ፤ከሚደርስብሽም ነገር እስቲ ያድኑሽ።

14 እነሆ፣ እነርሱ ገለባ ናቸው፤እሳት ይበላቸዋል፤ከነበልባሉ ወላፈን የተነሣ፣ራሳቸውን ማዳን አይችሉም።ሰው የሚሞቀው ፍም አይኖርም፤ተቀምጠው የሚሞቁትም እሳት የለም።

15 ከልጅነት ጀምሮ አብረሻቸው የደከምሽው፣አብረሽ የተገበያየሻቸው፣ሊያደርጉ የሚችሉት ይህንኑ ብቻ ነው።እያንዳንዱ በስሕተቱ ይገፋበታል፤አንቺን ግን የሚያድን የለም።