1 “የያዕቆብ ቤት ሆይ፤እናንት በእስራኤል ስም የተጠራችሁ፣ከይሁዳ ዘር የተገኛችሁ፣እናንት በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፣በእውነት ወይም በጽድቅ ሳይሆን፣የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ ይህን ስሙ!
2 እናንት የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤
3 የቀደሙትን ነገሮች ከብዙ ዘመን በፊት ተናግሬአለሁ፤ከአፌ ወጥተዋል፤ እንዲታወቁም አድርጌአለሁ፤እኔም ድንገት ሠራሁ እነርሱም፤ ተፈጸሙ።
4 የቱን ያህል እልኸኛ እንደ ነበርህ ዐውቃለሁና፤የዐንገትህ ጅማት ብረት፣ግንባርህም ናስ ነበር።
5 ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ገና ድሮ ነገርሁህ፤ከመፈጸማቸው በፊት አስታወቅሁህ፤ ይህም፣‘ጣዖቶቼ ይህን አደረጉ፤ከዕንጨት የተቀረጸው ምስልና ከብረት የተሠራው አምላኬ ይህን ወስኖአል’እንዳትል ነው።