ኢሳይያስ 54:1-7 NASV

1 “አንቺ መካን ሴት፤አንቺ ልጅ ወልደሽ የማታውቂ፤ዘምሪ፤ እልል በዪ፤ በደስታ ጩኺ፤አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣ባል ካላት ሴት ይልቅ፣የፈቷ ልጆች ይበዛሉና”ይላል እግዚአብሔር።

2 “የድንኳንሽን ቦታ አስፊ፤የድንኳንሽን መጋረጃዎች በትልቁ ዘርጊ፤ፈጽሞ አትቈጥቢ፤ገመዶችሽን አርዝሚአቸው፤ካስማዎችሽንም ቀብቅቢ።

3 ወደ ቀኝም ወደ ግራም ትስፋፊያለሽ፤ዘሮችሽ መንግሥታትን ይወርሳሉ፤በባድማ ከተሞቻቸውም ይኖራሉና።

4 “አይዞሽ አትፍሪ፤ ኀፍረት አይገጥምሽም፤ውርደት ስለማይደርስብሽ አትሸማቀቂ፤የወጣትነት ኀፍረትሽን ትረሺዋለሽ፤የመበለትነት ስድብሽንም ከእንግዲህ አታስታውሺውም።

5 ባልሽ ፈጣሪሽ ነውና፤ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ታዳጊሽ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።

6 እንደ ተናቀች የልጅነት ሚስት፣ከልብ እንዳዘነችና እንደ ተጠላች ሚስት፣ እግዚአብሔር እንደ ገና ይጠራሻል”ይላል አምላክሽ።

7 “ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።