ኢሳይያስ 57:9-15 NASV

9 የወይራ ዘይት ይዘሽ፣ሽቶ በላዩ ጨምረሽ ወደ ሞሎክ ሄድሽ፤መልእክተኞችሽን ወደ ሩቅ አገር ላክሽ፤እስከ ራሱ እስከ ሲኦልም ዘለቅሽ።

10 በመንገድ ብዛት ደከምሽ፤ነገር ግን ‘ተስፋ የለውም’ አላልሽም፤የጒልበት መታደስ አገኘሽ፤ስለዚህም አልዛልሽም።

11 “እኔን የዋሸሽኝ፤ማንን ፈርተሽ፣ ማንንስ ሠግተሽ ነው?እኔን ያላስታወስሽው፣ይህንንም በልብሽ ያላኖርሽው፣እኔን ያልፈራሽው፣ዝም ስላልሁ አይደለምን?

12 ጽድቅሽንና ሥራሽን አጋልጣለሁ፤እነርሱም አይጠቅሙሽም።

13 ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስቲ ያድኑሽ!ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ሽውሽውታም ይበትናቸዋል።እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ምድሪቱን ይወርሳል፤የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”

14 እንዲህ ይባላል፤“አብጁ፤ አብጁ፤ መንገድ አዘጋጁ፤ከሕዝቤ መንገድ ዕንቅፋት አስወግዱ።”

15 ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤“የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።