ኢሳይያስ 61:1-7 NASV

1 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል።ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ለምርኮኞች ነጻነትን፣ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል፤

2 የተወደደውን የእግዚአብሔርን ዓመት፣የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤

3 በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣በዐመድ ፈንታ፣የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣በልቅሶ ፈንታ፣የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስላቸው፣በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።

4 የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትንፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።

5 መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል።

6 እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።

7 ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ዕጥፍ ይቀበላሉ፤በውርደታቸው ፈንታ፣በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።