ኢሳይያስ 62:1-7 NASV

1 ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።

2 መንግሥታት ጽድቅሽን፣ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።

3 በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።

4 ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ነገር ግን፣ “ደስታዬ በእርሷ” ትባያለሽ፤ምድርሽም፣ “ባለ ባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ምድርሽም ባለ ባል ትሆናለች።

5 ጐልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣ልጆችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።

6 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም።እናንት ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤ፈጽሞ አትረፉ፤

7 ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።