ኢሳይያስ 63:3-9 NASV

3 “እኔ በመጭመቂያው ወይኑን ብቻዬን ረገጥሁ፤ከመንግሥታት ማንም ከእኔ ጋር አልነበረም፤በቍጣዬ ረገጥኋቸው፤በመዓቴም ጨፈለቅኋቸው፤ደማቸው በመጐናጸፊያዬ ላይ ተረጭቶአል፤ልብሴንም በክዬዋለሁ።

4 የበቀል ቀን በልቤ አለ፤የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአል።

5 ተመለከትሁ፤ የሚረዳ ግን አልነበረም፤የሚያግዝ ባለመኖሩም ተገረምሁ፤ስለዚህ የገዛ ክንዴ ድነትን አመጣልኝ፤የገዛ ቊጣዬም አጸናኝ፤

6 መንግሥታትን በቍጣዬ ረጋገጥሁ፤በመዓቴም አሰከርኋቸው፤ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ።”

7 የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ፣ስለሚመሰገንበት ሥራው፣እንደ ፍቅሩና እንደ ቸርነቱ መጠን፣ለእስራኤል ቤት ያደረገውን፣አዎን፣ ስላደረገው መልካም ነገር እናገራለሁ።

8 እርሱም፣ “ርግጥ ነው፤ እነርሱ ሕዝቤ ናቸው፤የማይዋሹኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለ።ስለዚህም አዳኝ ሆነላቸው።

9 በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ፤የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤በፍቅሩና በምሕረቱ ዋጃቸው፤በቀደመው ዘመን ሁሉ አነሣቸው፤ተሸከማቸውም።