ኢሳይያስ 65:13-19 NASV

13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ባሮቼ ይበላሉ፤እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ባሮቼ ይጠጣሉ፤እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤እናንተ ግን ታፍራላችሁ።

14 ባሮቼ፣ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ፤እናንተ ግን፣ልባችሁ በማዘኑ ትጮኻላችሁ፤መንፈሳችሁ በመሰበሩም ወዮ ትላላችሁ።

15 ስማችሁንም፣የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።

16 ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።

17 “እነሆ፤ እኔ፣አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤አይታወሱም።

18 ነገር ግን በምፈጥረው፣ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና።

19 በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።