1 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር የሚላችሁን ስሙ።
2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የአሕዛብን መንገድ አትከተሉ፤እነርሱ በሰማይ ምልክቶች ይታወካሉ፣እናንተ ግን በእነዚህ አትረበሹ።
3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ዛፍ ከጫካ ይቈርጣሉ፤አናጺም በመሣሪያው ቅርጽ ያበጅለታል፤
4 በብርና በወርቅ ይለብጡታል፤እንዳይወድቅም፣በመዶሻ መትተው በምስማር ያጣብቁታል።
5 ጣዖቶቻቸው በዱባ ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤የመናገር ችሎታ የላቸውም፤መራመድም ስለማይችሉ፣ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤ጒዳት ማድረስም ሆነ፣መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣አትፍሯቸው።”
6 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዳንተ ያለ ማንም የለም፤አንተ ታላቅ ነህ፤የስምህም ሥልጣን ታላቅ ነው።
7 የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ ሆይ፤አንተን የማይፈራ ማነው?ክብር ይገባሃልና።ከምድር ጠቢባን ሁሉ፣ከመንግሥቶቻቸውም ሁሉ መካከል፣እንዳንተ ያለ የለም።