ኤርምያስ 17:2-8 NASV

2 ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣በለመለሙ ዛፎች ሥር፣ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስል ያስባሉ።

3 በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣ለብዝበዛ አደርገዋለሁ።

4 በገዛ ጥፋትህ፣የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤በማታውቀውም ምድር፣ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ለዘላለም የሚነደውን፣የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።”

5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በሰው የሚታመን፣በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።

6 በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።

7 “ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።

8 በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”